27/07/2025
Epidural Labour Analgesia - ኤፒዱራል የምጥ ህመም ማስታገሻ
የምጥ ህመም አንዲት እናት ልጅን ለመውለድ በምታደርገው ሂደት ውስጥ የሚከሰት ተፈጥሯዊ ከፍተኛ የህመም አይነት ነው። ይህም በምጥ ወቅት በሚፈጠር የማህፀን መኮማተር ፣ የማህፀን በር መከፈት እንዲሁም ነርቭ ላይ በሚደረስ ጫና ይፈጠራል። ኤፒዱራል በምጥ ጊዜ የሚሰማን ከባድ ህመም ለማስታገስ የሚረዳ የማደንዘዣ አይነት ሲሆን ከሌሎቹ የህመም ማስታገሻ ዘዴዎች የተሻለ ተመራጭ እና ውጤታማ ነው።
🔴የኤፒዱራል አሰጣጥ ሂደት
የኤፒዱራል አሰጣጥ ሂደት በጥንቃቄ የሚከናወን ሲሆን የሚከተሉትን ያካትታል፦
➥ዝግጅቶች: የስምምነት ፊርማ መውሰድ ፣አስፈላጊ ምርመራዎችን ማድረግ፣ የታካሚዋን ሁኔታ መከታተያ መሳሪያዎችን ማድረግ እና መድሀኒቶችን ማዘጋጀትን ያጠቃልላል።
➥አቀማመጥ፦ እንድትቀመጥና ወደፊት እንድታጎነብስ ወይም በጎኗ እንድትተኛ ትደረጋለች።
➥ቦታውን ማጽዳትና ማደንዘዝ፦ መርፌው የሚወጋበት የታችኛው ጀርባ አካባቢ በአዮዲን እና በአልኮል ይጸዳል። ከዚያም ዋናው የኤፒዱራል መርፌ ሲገባ ህመም እንዳይሰማ በትንሽ መርፌ የቆዳውን ክፍል ብቻ የሚያደነዝዝ መድሃኒት ይሰጣል።
➥የኤፒዱራል መርፌውን "ኤፒዱራል ስፔስ" (Epidural Space) ወደሚባለው የአከርካሪ አጥንት ክፍል ማስገባት።
➥ቀጭን ቱቦውን (Catheter) ማስቀመጥ፦ በመርፌው ቀዳዳ በኩል ቀጭን የፕላስቲክ ቱቦ (ካቴተር) ወደ ኤፒዱራል ስፔስ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም መርፌው በጥንቃቄ ይወጣና ቱቦው ብቻ ጀርባ ላይ በፕላስተር ይለጠፋል።
➥መድሃኒቱን መስጠት፦ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቱ በቱቦው በኩል እንደ አስፈላጊነቱ በተወሰነ የጊዜ ልዩነት ይሰጣል። ህመሙ ሙሉ በሙሉ እስኪታገስ ድረስ ከ15-20 ደቂቃ ሊወስድ ይችላል።
🔴የኤፒዱራል ጥቅሞች
➥በምጥ ጊዜ የሚሰማን ከባድ ህመም በከፍተኛ ደረጃ ያስታግሳል።
➥ምጡ ለረጅም ሰዓት ከቆየ እናትየው እንድታርፍና ለመጨረሻው የምጥ ሂደት ጉልበት እንዲኖራት ይረዳታል።
➥በምጥ ጊዜ በቀዶ ህክምና መውለድ (C/S) ካስፈለገ ሌላ ማደንዘዣ ሳይሰጥ በዚሁ ካቴተር በኩል የማደንዘዣ መድሃኒት በመጨመር ቀዶ ህክምናውን ማከናወን ይቻላል።
➥ከወሊድ በኋላ የሚመጣ ድባቴን ይቀንሳል
🔴የጎንዮሽ ጉዳቶች
➥የደም ግፊት መቀነስ ሊኖር ይችላል
➥አንዳንድ እናቶች በሰውነታቸው ላይ የማሳከክ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል።
➥የእግር መክበድ ወይም መደንዘዝ : ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ የሚለቅ ነው።
➥አልፎ አልፎ ራስ ምታት ሊከሰት ይችላል።
➥ኢንፌክሽን
🔴የማይፈቀድበት ሁኔታ
➥ታካሚዋ ካልፈለገች
➥በቀላሉ ደም የመፍሰስ ችግር
➥ቱቦው የሚገባበት ቦታ ቁስል
➥የጭንቅላት ውስጥ ግፊት(በወጠር) በተለያየ ምክንያት
➥ከፍተኛ የሆነ የደም ግፊት መጠን ማነስ
ዶ/ር ዮሴፍ አንሙት: በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል
የአንስቴዦሎጂ እና ፅኑ ህክምና ስፔሻሊስት