27/07/2026
''የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከብሉይ ወደ ሐዲስ ኪዳን የተሸጋገረች እንጂ በመጤ ስደተኞች የተመሰረተች አይደለችም''
ለአህመዲን ጀበል የተሳሳተ ትረካ የተሰጠ ታሪካዊ ምላሽ
አህመዲን ጀበል «ክርስቲያኖች ተሰደው ሲመጡ ተቀበልናቸው» በሚል ርዕስ ባሰራጨው ጽሁፍ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን በ4ኛው ክፍለ ዘመን «በመጡ መጤ ስደተኞች የተሰበከች» አድርጎ ለማቅረብ ያደረገው ጥረት ፍጹም ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌለው ትረካ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ በ4ኛው ክፍለ ዘመን በስደተኞች የተጀመረ አዲስ እምነት ሳይሆን፣ ሀገራችን ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበራትን የብሉይ ኪዳን አምልኮ መሠረት በማድረግ በቀጥታ ወደ ሐዲስ ኪዳን የተሸጋገረችበት ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነታ ነው።
ኢትዮጵያ ከንግሥተ ሳባ ዘመን ጀምሮ የአንድ አምላክ (የእግዚአብሔር) እምነት የነበራት፣ በጣና ቂርቆስ፣ በአክሱም ጽዮን እና በሌሎችም ታሪካዊ ስፍራዎቿ የብሉይ ኪዳን መስዋዕት ይቀርብባቸው የነበሩ ቤተ መቅደሶች ያሏት ሀገር ነበረች። ይህ የብሉይ ኪዳን እምነትና አምልኮ ደግሞ ለሐዲስ ኪዳን ወንጌል መቀበል ዋናው ሀገር በቀል መሠረት ሆኗል።
ለዚህም ግልጽና መተኪያ የሌለው ማስረጃ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 8 (ቁጥር 26-40) ላይ የተመዘገበው የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ታሪክ ነው። የኢትዮጵያ ንጉሥ (የህንድኬ) ባላንደራ የነበረው ይህ ታላቅ ባለሥልጣን ወደ ኢየሩሳሌም ሂደው ከሚሰግዱትና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩት አንዱ ነበር። በሰረገላው ላይ ሆኖ ያነብ የነበረው ደግሞ የነቢዩ ኢሳይያስን መጽሐፍ (ብሉይ ኪዳንን)ነበር።
እዚህ ጋር መጠየቅ ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ ኢትዮጵያውያን እግዚአብሔርን የማያውቁና «ባዕድ እምነት ያላቸው» ቢሆን ኖሮ ይህ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን የብሉይ ኪዳንን መጽሐፍ ለምን ያነብ ነበር? ለምንስ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ነበር?
ሐዋርያው ቅዱስ ፊሊጶስ ጃንደረባውን ሲያጠምቀው፣ ክርስትናን እንደ አዲስ የውጭ እምነት አድርጎ አልሰበከውም። ይልቁንም ያነበው የነበረውን የብሉይ ኪዳን ትንቢት (ኢሳይያስ 53) መሠረት አድርጎ «ትንቢቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጸመ» ብሎ በማስረዳት ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን እንዲሸጋገር አደረገው እንጂ። ጃንደረባውም ደስ ብሎት ወደ ሀገሩ ተመልሶ የክርስቶስን ወንጌል በሀገሩ አስተምሯል።
ይህ የሚያሳየው ክርስትና በኢትዮጵያ በ330 ዓ.ም «በመጤ ስደተኞች» የተበሰረ ሳይሆን፣ ከወንጌል መባቻ (ከ1ኛው ክፍለ ዘመን) ጀምሮ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን አማካይነት የገባና ከብሉይ ኪዳን እምነታችን ጋር የተያያዘ ሀገር በቀል የዕምነት ሽግግር መሆኑን ነው።
በ4ኛው ክፍለ ዘመን በአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ) አማካይነት የተከናወነው ተግባርም፣ ክርስትናን አዲስ እምነት አድርጎ ማምጣት ሳይሆን፣ በጃንደረባው ዘመን ጀምሮ በሀገር ውስጥ ይንቀሳቀስ የነበረውን የሐዲስ ኪዳን እምነት በአክሱም ቤተ-መንግሥትና በህዝቡ ዘንድ ይፋዊ የሀገር መንግሥት ሃይማኖት እንዲሆን የማደራጀትና የማጠናከር ሥራ ነው።
ፍሬምናጦስም ቢሆን የመጣው በስደት ሳይሆን በባህር ጉዞ አደጋ ምክንያት አክሱም ገብቶ በአክሱም ቤተ-መንግሥት ያደገ፣ የንግሥት እና የንጉሥ ኢዛና አማካሪና አስተማሪ የነበረ ሰው ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሀገር ግንባታ ውጭ እንደነበረች አድርጎ ማቅረብ ታሪክን የመካድ ያህል ነው።
የኢትዮጵያ ፊደል (ግዕዝ) የቁጥር፣ የዜማና የጽሁፍ ስርዓት አግኝቶ እንዲያድግና እስከ ዛሬ ሀገራዊ ማንነታችን ሆኖ እንዲቀጥል ያደረገችው ቤተክርስቲያን ነች።
«ፍትሐ ነገሥት»ን ጨምሮ በርካታ ህጋዊና አስተዳደራዊ ስርዓቶች የሀገሪቱ የህግ መሰረት ሆነው ያገለገሉት በቤተክርስቲያኗ አማካይነት ነው።
ከውጭ ወረራዎች ጋር በተደረጉ አገራዊ ተጋድሎዎች ውስጥ ቤተክርስቲያን የህዝብ አንድነትና የሀገር ፍቅር ማዕከል ሆና አገልግላለች።
በአክሱም፣ በዛግዌ፣ እና በሰሎሞናዊው ሥርወ-መንግሥት ዘመናት ኢትዮጵያ የምትታወቀውና የምትመራው በቤተክርስቲያኗና በመንግሥት የጠበቀ ትብብር ነበር።
ይህ ማለት ቤተክርስቲያን የሀገሪቱ ምሰሶና ግንባር ቀደም አካል እንጂ «መጤ» ልትባል አትችልም።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከብሉይ ኪዳን እስከ ሐዲስ ኪዳን የዘለቀች፣ የሀገሪቱን ፊደል፣ ህግ፣ ስልጣኔና መንግሥታዊ መዋቅር የገነባች የሀገር ምሰሶ እንጂ «በመጤ ስደተኞች የተመሰረተች» አይደለችም።
የጋራ ሀገር ለመገንባት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የሀገሪቱን ታሪክ የቤተክርስቲያኗን መሰረታዊ የታሪክ ሚና እና ሀገር የመስረት ታሪኳን በማደብዘዝ ወይም «መጤ» በማለት የሚደረግ አካሄድ ታሪካዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትነት የለውም የጋራ አብሮነትንም አይጠቅምም።
የኔታ
ሰላም ለኢትዮጲያ
ሰላም ለህዝባችን
ወሎ አዲስ የህዝብ አድማስ