Dr Abera Etana

Dr Abera Etana በቀላሉ ልትረዷቸው እና ልታውቋቸው የሚገቡ ጤና ጤና ነክ መረጃዎችን የምታገኙበት ገጽ ነው

♦️ የወለድሻት ልጅ በርግጥም ልጅሽ ሳትሆን "እህትሽ" ብትሆንስ?? 🧬🤯👉 ዶክተሮች የገዛ ልጅህ አባት አይደለህም ቢሉህ ምን ይሰማሃል?👉 አምጠሽ የወለድሻት ልጅ በርግጥም አባቷ ባለቤትሽ እን...
27/03/2026

♦️ የወለድሻት ልጅ በርግጥም ልጅሽ ሳትሆን "እህትሽ" ብትሆንስ?? 🧬🤯

👉 ዶክተሮች የገዛ ልጅህ አባት አይደለህም ቢሉህ ምን ይሰማሃል?
👉 አምጠሽ የወለድሻት ልጅ በርግጥም አባቷ ባለቤትሽ እንደሆነ ቢረጋገጥም፣ ያለምንም ጥርጥር "አንቺ እናቷ አይደለሽም" ብትባይ በድንጋጤ ራስሽን ትስቺ ይሆን?

ይህ በሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም ላይ የታየ ታሪክ ሳይሆን፣ በተጨባጭ በሁለት የተለያዩ ቤተሰቦች ላይ የደረሰ እውነተኛ እና አስገራሚ የህክምና ክስተት ነው! 🇺🇸✨

1️⃣ የሊዲያ ፋየርቺልድ (Lydia Fairchild) አስደንጋጭ ገጠመኝ 🔹
በዋሽንግተን ግዛት የምትኖረው የ26 ዓመት እናት ሊዲያ፣ የመንግሥት ዕርዳታ ለማግኘት ስታመለክት የዲኤንኤ (DNA) ምርመራ እንዲደረግ ታዘዘች። ነገር ግን ውጤቱ ሲመጣ አለምን የሚያዞር ነበር፦
✅ የልጆቹ አባት? ፍቅረኛዋ መሆኑ ተረጋገጠ።
✅ ልጆቹ? እርስ በርሳቸው ወንድማማችና እህትማማች መሆናቸው ተረጋገጠ።
❌ ሊዲያ? እንደ ዲኤንኤ ውጤቱ ከሆነ — እሷ የልጆቹ እናት አይደለችም! 🚫
ሊዲያ በድንጋጤ ተዋጠች። ልጆቹን በማኅፀኗ ተሸክማ እንደወለደቻቸው ታውቃለች፤ ነገር ግን በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ከእናትነት ወደ "ወንጀለኛ ተጠርጣሪነት" ተቀየረች። አቃቤ ህግ በማጭበርበር ወንጀል ከሰሳትና ፍርድ ቤት አቆማት፣ ልጆቿንም ሊነጥቃት ጫፍ ደርሶ ነበር። ⚖️⚠️

እውነታው ሲገለጥ፦ አንዲት አስተዋይ ጠበቃ ሊዲያ በሰውነቷ ውስጥ "ሁለት አይነት የዲኤንኤ ዘር" እንዳላት ደረሰችበት። ደሟ አንድ አይነት ዘረመል (ዲኤንኤ) ሲኖረው፣ እንቁላል ማምረቻዋ (Ovaries) ደግሞ ሌላ የተለየ ዘረመል (ዲኤንኤ) ነበረው። ይህ የሆነው ገና ሳትወለድ በማህፀን ውስጥ እያለች ያልተወለደችው የመንታ እህቷ ዘረመል ከ ሊዲያ አካል ጋር በመዋሃዱ ነበር። ለልጆቿ የሰጠችው የራሷን ሳይሆን ያልተወለደችውን የእህቷን ዘረመል (ዲኤንኤ) ነበር ማለት ነው:: ዘጠኝ ወር ተሸክማ አምጣ ብትወልዳቸውም ልጆቹ የእህቷ እንጂ የሷ አይደሉም ማለት ነው: ሴት ልጇ ደሞ ጭራሽ ልጅ ሳትሆን እህት ልትባል ነው! 💡
2️⃣ "አጎት" የሆነው አባት ታሪክ (እ.ኤ.አ 2014) 🔹
አንድ ባልና ሚስት በህክምና እርዳታ (Fertility Clinic) ጤናማ ወንድ ልጅ ወለዱ። ነገር ግን የልጁ የደም አይነት ከወላጆቹ ጋር ሊገጥም አልቻለም። ግራ የተጋቡት ወላጆች የዲኤንኤ ምርመራ ሲያደርጉ ውጤቱ፦ "አባትየው የልጁ ባዮሎጂካዊ አባት አይደለም" የሚል ሆኖ ተገኘ። 😱

ወላጆቹ "ክሊኒኩ የሌላ ሰውን የዘር ፍሬ ተጠቅሞብኛል" በሚል ክስ መሰረቱ። ነገር ግን ክሊኒኩ "ምንም ስህተት አልተፈጠረም" በማለት ተከራከረ። በባለትዳሮቹ መካከል ሊፈጠር የሚችለውን ጥርጣሬና እስቲ አስቡት! ⚖️

ቤተሰቡ ወደ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ዘንድ ሄዱ። ጥልቅ ምርመራ ሲደረግ እጅግ እንግዳ ውጤት መጣ፦ "ይሄ አባት የልጁ አባት ሳይሆን አጎቱ ነው!" የሚል ነበር :ነገር ግን ይሄ አባት ፈጽሞ ወንድም አልነበረውም ነገር ግን በተደረገ ተጨማሪ ምርመራ አባትየው በሰውነቱ ውስጥ ከአንድ በላይ የዘረመል (የ ዲኤንኤ) አይነት እንደያዘ ተረጋገጠ። ለምርመራ የተወሰደው የምራቅ ናሙና ከአባቱ ጋር ባይገጥምም፣በአባቱ የዘር ፍሬ (S***m) ውስጥ ያለው ዘረመል ግን ከልጁ ጋር 100% ይገጥም ነበር። በሳይንሳዊ አገላለጽ፣ የልጁ አባት በፅንስ ደረጃ ሳይወለድ የቀረው የአባትየው "መንታ ወንድም" ነው ማለት ነው! 🔍✨

🧬 ሳይንሳዊ ትንታኔው ምንድን ነው?

ይህ አስገራሚ ሁኔታ "ሂውማን ቺሜራ" (Human Chimera) ይባላል። ይህ የሚሆነው በእናታቸው ማህፀን ውስጥ ሳሉ መንትያ ሆነው ከተረገዙ በኃላ፣ አንደኛው ፅንስ ገና በጅምር ላይ እያለ የሌላኛውን መንትያ ጽንስ ሴሎች (Cells) ጠቅልሎ ወደ ራሱ ሲያስገባ ነው።
በዚህም ምክንያት በአንድ ሰው ውስጥ ሁለት የተለያዩ የዘረመል አይነቶችን ይኖራሉ ማለት ነው ።
ልዩነቱ፦ የምራቅ ወይም የደም ዘረመል ከአንድ ሰው ቢመጣ፣ የዘር ፍሬ ወይም እንቁላል ውስጥ የሚገኘው ዘረመል ግን ከሌላ (ካልተወለደው መንትያ) ሊመጣ ይችላልማለት ነው።

♦️ለዚህ ክስተት ለምን ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል?

👉ከ 8 ነጠላ ሆነው ከሚወለዱ ልጆች ውስጥ አንዱ በመጀመሪያው ደረጃ ላይ መንትያ የመሆን ዕድል ሊኖራቸው ይችላል። ይህም ማለት "ቺሜሪዝም" የሚባለው ክስተት እኛ ከምናስበው በላይ በሰዎች ላይ በብዛት ሊከሰት ይችላል።
👉የዲኤንኤ ምርመራዎች ይህንን ሁኔታ በቀላሉ ስለማያሳዩ፣ በቤተሰቦች ላይ ህጋዊ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውስ ሊፈጥሩ ይችላሉ።

👉 ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
📍 የቤተሰብ ጽናት፦ እነዚህ ወላጆች በምርመራ ውጤቱ ተሸንፈው እርስ በርስ ከመጠራጠር ይልቅ፣ እውነቱን ለማግኘት እስከመጨረሻው መታገላቸው ቤተሰባቸውን አድኖታል። ❤️
📍 የህክምና ጥንቃቄ፦ ቴክኖሎጂ እያደገ ቢመጣም፣ የሰው ልጅ አካል አሁንም እኛ ካወቅነው በላይ እጅግ ምስጢራዊ መሆኑን ያሳያል።
ምናልባትም ዛሬ ዓለም ላይ ብዙ አባቶች ወይም እናቶች ባልተወለደ መንትያቸው ዲኤንኤ ምክንያት ብቻ ከገዛ ልጆቻቸው ጋር እንደማይዛመዱ ተነግሯቸው በስህተት ተፈርዶባቸው ሊሆን ይችላል! 💔

💬 እንዲህ አይነት ነገር በእርስዎ ወይም በሚያውቁት ሰው ላይ ቢደርስ ምን ያደርጋሉ? በዲኤንኤ ምርመራ ላይ ያለዎት እምነትስ አሁንም እንደቀድሞው ነው?

ሀሳባችሁን በኮሜንት አጋሩን! 👇

😄Enjoy the Crazy picture 😄

Dr Abera Etana
#ሐዋሳ #የህክምናምስጢር

👶 የሕፃናት ተቅማጥ በያዛቸው ቁጥር ሽሮፕ መስጠት ትክክል ነው?! 🍼በሕፃናት ላይ የሚከሰት ተቅማጥ በአግባቡ ከተያዘ በቀላሉ የሚድን ቢሆንም፣ በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ለከፍተኛ ድርቀት እ...
02/03/2026

👶 የሕፃናት ተቅማጥ በያዛቸው ቁጥር ሽሮፕ መስጠት ትክክል ነው?! 🍼

በሕፃናት ላይ የሚከሰት ተቅማጥ በአግባቡ ከተያዘ በቀላሉ የሚድን ቢሆንም፣ በቂ ጥንቃቄ ካልተደረገ ግን ለከፍተኛ ድርቀት እና ለህይወት አስጊ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል።
⚠️ የተሳሳቱ ልማዶችና ማስጠንቀቂያዎች
🛑 "ግግ ማስነቀል" (Gigg Removal)፦ ተቅማጥ ከጥርስ ወይም ከ"ግግ" ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ይልቁንም ግግ ማስነቀል ለከፍተኛ ኢንፌክሽን (Sepsis) እና ለደም መፍሰስ ይዳርጋል። ❌
🛑 ባክቴሪየም (Bactrim/Bacterium)፦ አብዛኛው ተቅማጥ የሚመጣው በቫይረስ ስለሆነ፣ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ አንቲባዮቲክ (Antibiotics) መስጠት የልጁን የምግብ መፈጨት ሥርዓት ይበልጥ ያበላሸዋል።
🩺 የቤት ውስጥ የመጀመሪያ እርዳታ (Home Care)
ልጅዎ ተቅማጥ ሲኖረው ዋናው ግባችን ፈሳሽ እንዳይቀንስ መከላከል ነው፡
🔹 ቶሎ ቶሎ ማጥባት፦ የእናት ጡት ወተት ተቅማጥን የመከላከልና ድርቀትን የማስቆም ተፈጥሯዊ አቅም አለው። 🤱
🔹 ተጨማሪ ፈሳሾች፦ እንደ አጥሚት እና ሾርባ ያሉ ፈሳሾችን በብዛት መስጠት።
🔹 ORS (የጨውና ስኳር መፍትሄ)፦ ህፃኑ ባስቀመጠ ቁጥር በቂ ORS መስጠት ግድ ይላል።
🔹 ዚንክ (Zinc Supplement)፦ አዳዲስ የህክምና መመሪያዎች እንደሚያሳዩት ለ10-14 ቀናት የሚሰጥ የዚንክ ታብሌት ወይም ሽሮፕ ተቅማጡ ቶሎ እንዲያቆም እና ለወደፊትም እንዳይመለስ ይረዳል። ✅
🚨 በፍጥነት ወደ ህክምና መሄድ ያለብዎት መቼ ነው? (Danger Signs)
ከሚከተሉት ምልክቶች አንዱ እንኳን ከታየ ሳይዘገዩ ወደ ጤና ተቋም ይውሰዱ፡
📍 የማያቋርጥ ትውከት፦ ምንም አይነት ፈሳሽም ሆነ ምግብ መውሰድ ካልቻለ።
📍 የድርቀት ምልክቶች፦ የአይን መጎድጎድ፣ የእርግብግቢት (Fontanelle) መስመጥ ወይም ቆዳን ቆንጥጦ ሲለቁት ቶሎ አለመመለስ። 📉
📍 ድካም እና መዝለፍለፍ፦ ህፃኑ በጣም ከደከመ ወይም ከወትሮው በተለየ እንቅልፍ እንቅልፍ ካለው።
📍 የደም ተቅማጥ፦ ሰገራው ላይ ደም ከታየ (ይህ የባክቴሪያ ምልክት ሊሆን ስለሚችል አፋጣኝ ህክምና ይፈልጋል)። 🩸
📍 ከፍተኛ ትኩሳት እና የሆድ መነፋት።
💡 የዶክተር መልዕክት
ተቅማጥ በራሱ ጊዜ የሚያቆም (Self-limiting) ቢሆንም፣ ወላጆች ትኩረት ማድረግ ያለባቸው ህፃኑ የፈሳሽ እጥረት እንዳይገጥመው መከላከል ላይ ነው። በባህላዊ ህክምና ጊዜ በማባከን የልጆችን ህይወት አደጋ ላይ አንጣል።
ጥያቄ ካላችሁ ኮመንት ላይ አስቀምጡልኝ። የልጆች ጤና የሀገር ተስፋ ነው! 🏥👨‍⚕️

ዶ/ር አበራ ኢታና (Dr. Abera Etana)

DrAbera Etana


#የህፃናትጤና #ተቅማጥ #ጤና #የእናቶችምክር #ኢትዮጵያ #ዶክተርአበራ #ተቅማጥእናህፃናት #ጥንቃቄ

❤️ከምጥ የበረታ የአንዲት እናት የ14 ዓመታት የእንባ፣ የፈተና እና የፅናት ጉዞ❤️ምዕራፍ 1፡ "ከእናት ጡት ውጪ አትስጪ" የተባለው ገዳይ ትዕዛዝ""ውድ ዶክተር፤ የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ ...
02/03/2026

❤️ከምጥ የበረታ የአንዲት እናት የ14 ዓመታት የእንባ፣ የፈተና እና የፅናት ጉዞ❤️

ምዕራፍ 1፡ "ከእናት ጡት ውጪ አትስጪ" የተባለው ገዳይ ትዕዛዝ"

"ውድ ዶክተር፤ የመጀመሪያ ልጄን ስወልድ የ18 ዓመት ታዳጊ ነበርኩ። ይሄ የሆነው ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት ነው። ልጄን በሆዴ ከያዝኩበት ቀን ጀምሮ እኩያ ልጅ ይኖረኛል በሚል ጉጉት ብዙ አስቸጋሪ ነገሮችን ተቋቁሜ የምወልድበት ቀን ደረሰ። ምጡ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በሰላም የምታሳሳ ቆንጅዬ ህፃን ታቅፌ ወደ ቤት ከመመለሴ በፊት ከሐኪሞች አንድ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጠኝ፦ 'ከእናት ጡት ውጪ ምንም አይነት ነገር እንዳትሰጫት!'

እኔም ሞኝ እንደመከሩት፣ ልጄን ይዤ ወደ ቤት ስገባ ጡቴ ወተት የሚባል ነገር አልነበረውም። ህፃኗ በረሃብ ታለቅሳለች፤ እኔ ግን ሐኪም ያዘዘኝን ትዕዛዝ የሙጥኝ ብዬ ከጡቴ ጋር እታገላለሁ። በዚህ መሃል ልጄ በረሃብ እና በፈሳሽ እጥረት ደከመች፤ አይኔ እያየ ላጣት ሆነ🥹።

ወዲያው ወደ አንድ የህፃናት ስፔሻሊስት ይዣት ሄድኩ። ሐኪሙ ለሶስት ቀን የምትሆን ጨቅላ ህፃንን አንዴ በእጇ፣ አንዴ በእግሯ፣ አንዴ በጭንቅላቷ ላይ መርፌ እየቀያየረ ግሉኮስ ሲሰጣት ሁለት ቀን አሳደራት። በመጨረሻም እንደማትተርፍ ሲያምን፣ 'መንገድ ላይ ታርፋለች፤ ይዛችኋት ሌላ ሆስፒታል ሂዱ' ብሎ አሰናበተን። ወደ ቤት ስንመለስ እናቴ ልጄን ተቀብላ 'የኔ ቅዱስ ገብርኤል አያስደነግጥብኝም' እያለች እና አምላኳን እየለመነች፣ ሰዎች 'ሞታለች' ብለው ተሰብስበው ከሚያለቅሱበት ቦታ ላይ አፏ ላይ እምነት እና ፀበል እያደረገች ታክሲ ጠርታ ወደ ወለድኩበት ሆስፒታል ይዘናት ሄድን።

እንዳዩዋት ተረባረቡባት፤ ችግሩ የምግብ እጥረት እንደሆነ አወቁ። 'ከፈጣሪ ጋር የቻልነውን እናደርጋለን' ብለው ቃል ገብተው፣ ጡቴን እያለቡ በአፍንጫዋ በተሰካ ቱቦ አማካኝነት መስጠት ጀመሩ። መጥባት እንዳትረሳ ደግሞ በየሰከንዱ ጡቴን አፏ ጋ እያስጠጋሁ እንድትሞክር ነገሩኝ። ሳልሰለች እያደረግኩ በሳምንቴ ልጄን ይዤ ወደ ቤቴ ገባሁ።"

ምዕራፍ 2፡ ጤናማዋ በሽተኛ (የምርመራው ግራ መጋባት)

"ከዛ በኋላ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ ተጀመረ። ስትወለድ ንቁ የነበረችው ህፃን፣ ክብደቷ አይጨምርም፤ እንደ እድሜ እኩዮቿ ምንም አይነት ለውጥ አታሳይም። ጉዞ ወደ ህክምና ተጀመረ። የሐኪሞች ምላሽ ግን 'ምንም ችግር የለባትም፣ በትክክለኛው እድገት ላይ ናት' የሚል ሆነ።

አንድ አመት አለፈ፣ ወራት ተጨመሩ፤ ምንም ለውጥ የለም። እድሜዋ እና ሁኔታዋ በፍፁም አይገናኝም። ተጨማሪ ምርመራ ያስፈልጋል ተባልኩ። የአይን ህክምና ተደረገ፣ 'ምንም የእይታ ችግር የለባትም' ተባልኩ። ነገር ግን ልጄ ስናወራት እንደሚያይ ህፃን ምንም ምላሽ አትሰጥም።

MRI እና EEG እንዲሰራ ወደ አዲስ አበባ ሪፈር ተባልኩ። አቅሙ ስላለኝ ወርጄ አሰራሁ። የላብራቶሪ ውጤቱ አሁንም 'ምንም አይነት የጤና እክል የለባትም፤ በትክክለኛው የእድገት ደረጃ ላይ ትገኛለች' የሚል ቀልድ የሚመስል እውነታ ይዞ መጣ። አስቡት! የሁለት ዓመት ህፃን ሆና ራሷን ችላ አትቀመጥም፣ አንገቷን አትሸከምም፣ ማንንም አትለይም... ነገር ግን ወረቀቱ 'በትክክለኛው እድገት ላይ ናት' ይላል። ፌዝ ይመስላል ግን ያኔ የገጠመኝ እውነት ነበር። አምኖ ቀን ከመጠበቅ እና ነገን ተስፋ ከማድረግ ውጭ ምንም ማድረግ አልቻልኩም።"

ምዕራፍ 3፡ የሰባት ዓመት የእንቅልፍ ጦርነት እና የሚጥል በሽታ

"እንኳን ለውጥ ቀርቶ እንቅልፍ የሚባል ነገር ከቤታችን ጠፋ። በፀበል በማመላለስ ትንሽ ለውጥ ታየ። በሶስተኛ አመቷ አንገቷን መሸከም፣ ራሷን ችላ መቀመጥ እና ከተኛችበት መነሳት ጀመረች🙏። ግን ከአመት አመት ለሰባት ዓመታት እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኗ አይዞርም ነበር።

ይህ አልበቃ ብሎ ሌላ ፈተና መጣ። ማስደንገጥ እና ራሷን ማሳት (የሚጥል በሽታ ምልክት) ጀመራት። አሁንም ወደ ህክምና ተቋም፣ አሁንም በድጋሚ MRI ተሰራ... ውጤቱ 'ከሚጥል በሽታ ውጭ እድገቷ ላይ ችግር የለበትም' የሚል ሆነ። የምናየው ሌላ፣ የምንሰማው ሌላ!"

ምዕራፍ 4፡ የመድሃኒቱ ፈተና እና የእናታዊ ስሜት (Intuition)

"የሚጥለውን መድሃኒት ገዝቼ ወደቤት ስገባ ሌላ ፈተና ጠበቀኝ። ክኒኑን ለአራት ከፍዬ 1/4ኛውን ብቻ እንድሰጣት፣ አለበለዚያ መጠኑ በዝቶ (Overdose) ህፃኗን እንደሚጎዳት ተነገረኝ። ክኒኑን ለአራት መክፈል እጅግ አስቸጋሪ ስለነበር ተመልሼ ሐኪሙ ጋ ሄድኩ። ሐኪሙም 'አማራጭ ስለሌለ በቀን ሁለቴ የምትወስደውን ትተሽ በቀን አንዴ ግማሹን (1/2) ስጫት' አለኝ።

መድሃኒቱን ከጀመረች በኋላ ማስደንገጡ እና መጣሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባባሰባት። በፊት እንቅልፍ ባይወስዳትም ዝም ብላ ትተኛ ነበር፤ አሁን ግን መድሃኒቱ እረፍት ነሳት፣ ማልቀስ እና መነጫነጭ መጣ። ከአጠገቧ መለየት አደጋ ሆነ።

ተመልሼ ሐኪሙ ጋ ሄጄ የሆነውን ስነግረው፣ 'አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይከሰታል፤ አሁን የምናደርገው የመድሃኒቱን መጠን መጨመር ነው፣ ሙሉውን ትውሰድ' አለኝ! ግራ ገባኝ። 'ባለፈው ግማሽ ክኒን ስትወስድ ይበዛባታል ብለህ ስትጨነቅ አልነበር? አሁን ሙሉውን ስትወስድ የጉዳት መጠኑን አይጨምረውም ወይ?' ብዬ ጠየቅኩት። ሐኪሙ 'ታዲያ ምን ይደረግ?' አለኝ።

'የሚደረገውማ እኔ አይኔ እያየ ተጨማሪ ጉዳት እና ስቃይ ልጄ ላይ አለመጨመር ነው' ብዬ በሆዴ ወስኜ ወጣሁ። መድሃኒቱን አቆምኩት። በባህላዊ ህክምና ሙከራ ጀመርኩ።

አምላክ ይመስገን... ከስምንት ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ልጄ አይኗን ከድና ተኛች! ይህ ለኛ ቤት ምን ማለት እንደሆነ የሚያውቀው አብሮን የኖረ ብቻ ነው። ያኔ ለስንት ሰው እንደተደወለ፣ የነበረን ደስታ ልዩ ነበር።"

ምዕራፍ 5፡ የሴትነት ፈተና እና የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት

"ሁሌም ለብቻዬ የሚያስለቅሰኝ እና ሰላም የሚነሳኝ አንድ ትልቅ ጭንቀት ነበር... 'ልጄ ለአቅመ ሔዋን ስትደርስ (የወር አበባ ስታይ) ምን እሆናለሁ?' የሚል ፍርሃት። ዳይፐር ላይ የምትፀዳዳ፣ ንፅህናዋን የማትለይ ልጅ፣ የሴትነት ባህሪ ሲመጣባት እንዴት እወጣዋለሁ እያልኩ እጨነቅ ነበር። በሷ ልክ የሚሆን ዳይፐር ማግኘት ራሱ ሌላ ፈተና ነበር።

ሆኖም ፈጣሪ እኔ ማን እንደሆንኩ ያውቃልና አበረታኝ። የፈራሁት የወር አበባ በ11 ዓመቷ መጣ፤ ሲመጣ ግን እኔ እንደፈራሁት አይነት ጭንቀት አልነበረም። እግዚአብሔር አቀለለው። እና እነሆ የካቲት 4 ቀን፣ 14ኛ ዓመቷን ያዘች🙏 እኔ ከፈለኩት በላይ የፈጣሪ ስራ መልካም ነው።"

ምዕራፍ 6፡ ምስጋና ለሰውም፣ ለፈጣሪም

"ይሄንን ሁሉ ስልህ ግን፣ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች ሚና ቀላል አልነበረም። የሽንገላ ሳይሆን የምር ከልቤ ቤተሰቦቼን አመሰግናለሁ። አስበው... እዚህ ሁሉ መከራ ላይ ሌላ ችግር ቢኖር? ጓደኞቼ ቢያገሉኝ፣ የትዳር አጋሬ ጥሎኝ ቢሄድ፣ ቤተሰቤ ባይረዳኝ ምን እሆን ነበር? እዚህ ላይ ነው የፈጣሪን ቸርነት እና ለኔ ምን ያህል እንደሚሳሳልኝ ያየሁት። ፈጣሪ በነሱ ላይ አድሮ አገዘኝ።

ዶክተር፣ ስላዳመጥከኝ እና ጊዜ ስለሰጠኸኝ አመሰግናለሁ!"
---
♦️♦️ውድ ወላጆች ከዚህ አስደናቂ ታሪክየተማራችሁትን ትልቅ ትምህርት እና የተመለከታችሁትን ክፍተት ነቅሳችሁ በማውጣት መደረግ የነበረበትን ነገር በሰከነ መንገድ ኮሜንት ላይ እንወያይ

🙏Please SHARE እና LIKE በማድረግ ብዙዎች እንዲማሩበት እናድርግ

Dr Abera Etana

🛑 የብልት አለመቆም ችግር ፡ ማንኛውም ወንድ (እና የትዳር አጋር) ሊያውቀው የሚገባ! 🛑🗣️ (እባክዎ ሼር ያድርጉ፤ ዝምታ እና ሃፍረት ከራሱ ከችግሩ በላይ እጅግ አደገኛ ናቸው 〰️〰️〰️〰️...
02/03/2026

🛑 የብልት አለመቆም ችግር ፡ ማንኛውም ወንድ (እና የትዳር አጋር) ሊያውቀው የሚገባ! 🛑

🗣️ (እባክዎ ሼር ያድርጉ፤ ዝምታ እና ሃፍረት ከራሱ ከችግሩ በላይ እጅግ አደገኛ ናቸው

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

1️⃣. የብልት አለመነሳት ምንድን ነው? 🤷‍♂️

የህክምና አጠራሩ Erectile Dysfunction (ED) ይባላል።
ትርጉሙም፡- ለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት በቂ በሆነ ደረጃ የብልት መቆም አለመቻል፣ ወይም ቆሞ ማቆየት አለመቻል ማለት ነው።

📌 ዋና ዋና ነጥቦች፡
- አልፎ አልፎ መከሰቱ ፡ እጅግ የተለመደ እና ኖርማል ነው።
- ለሳምንታት እና ወራት ያለማቋረጥ ከቀጠለ ፡ ዝም ብሎ የሚታለፈ አጋጣሚ አይደለም። ህክምና አለው!

📊 ጥናቶች እንደሚያሳዩት፡
- ከ40 እስከ 70 ዓመት ባሉ ወንዶች ውስጥ እስከ ግማሽ የሚሆኑት በተለያየ ደረጃ ይህ ችግር ያጋጥማቸዋል።
- ወጣት ወንዶችም ቢሆኑ በችግሩ ሊጠቁ ይችላሉ።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

2️⃣. በተፈጥሮ የብልት መቆም ሂደት እንዴት ይከናወናል? ⚙️

አንድ ጤናማ የብልት መቆም እንዲኖር የሚከተሉት ነገሮች መሟላት አለባቸው፡
🩸 ጤናማ የደም ስሮች
🧠 ጤናማ የነርቭ ስርዓት
🧬 የተስተካከለ ሆርሞን ፡ በተለይም ቴስቶስትሮን
🧘‍♂️ ጤናማ ስነልቦና

ከነዚህ ውስጥ የትኛውም በከፍተኛ ሁኔታ ከተስተጓጎለ፣ የስንፈተ ወሲብ ችግር ይከሰታል።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

3️⃣. ዋነኛ የስንፈተ ወሲብ መንስኤዎች 🔍

ሀ. አካላዊ መንስኤዎች 🏥
እነዚህ በተለይ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ በጣም የተለመዱ ናቸው፡

- የደም ስር እና የደም ዝውውር ችግሮች ፡ የልብ ህመም፣ ከፍተኛ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ ኮሌስትሮል፣ የስኳር ህመም፣ የደም ስሮች መጥበብ።
- የነርቭ ችግሮች ፡ ለረጅም ጊዜ የቆየ የስኳር ህመም (ነርቭን ይጎዳል)፣ የአከርካሪ አጥንት ጉዳት፣ የዳሌ አካባቢ ወይም የፕሮስቴት ቀዶ ጥገና፣ የነርቭ በሽታዎች (እንደ ፓርኪንሰንስ ያሉ)።
- የሆርሞን ችግሮች ፡ የቴስቶስትሮን ማነስ፣ የእንቅርት (ታይሮይድ) ችግሮች፣ የፕሮላክቲን ሆርሞን መብዛት።
- የመድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት:- አንዳንድ የደም ግፊት መድሃኒቶች፣ የድብርት መድሃኒቶች፣ የፕሮስቴት እና የሚጥል በሽታ መድሃኒቶች።
- የኑሮ ዘይቤ፡- ሲጋራ ማጨስ፣ ከልክ ያለፈ አልኮል መጠጣት፣ አደንዛዥ እጾች መውሰድ፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ የእንቅልፍ እጦት ወዘተ።

ለ. ስነ-ልቦናዊ እና የግንኙነት መንስኤዎች 🧠💔
አካል እና አእምሮ የተቆራኙ ናቸው። በነዚህ ስነልቦናዊ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡
- ጭንቀት (የስራ፣ የገንዘብ፣ የቤተሰብ)
- ፍርሃት (በተለይ "ግንኙነቱን በሚገባ ማከናወን እችል ይሆን?" የሚል የአፈፃፀም ፍርሃት - Performance Anxiety)
- ድብርት (Depression)
- ያለፈ መጥፎ ትዝታ ወይም ፆታዊ ጥቃት
- ከትዳር አጋር ጋር አለመግባባት፣ መተማመን ማጣት፣ ግልፅነት ማጣት
- ከፖርኖግራፊ ጋር የተያያዙ ችግሮች (ከእውነተኛ የትዳር አጋር ጋር ስሜት ለመፍጠር መቸገር)

አብዛኛውን ጊዜ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ መንስኤዎች በጋራ ይከሰታሉ። ለምሳሌ ቀለል ያለ አካላዊ ችግር ያለበት ሰው አንድ ቀን ሳይሳካለት ሲቀር ይጨነቃል፤ ያ ጭንቀት ደግሞ ችግሩን የባሰ ያደርገዋል።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

4️⃣. ስንፈተ ወሲብ የልብ ህመም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊሆን ይችላል! ⚠️🫀

ይህ ነጥብ እጅግ ወሳኝ እና ብዙ ጊዜ ችላ የሚባል ነው፡
- የደም ስርን የሚደፍኑ ችግሮች (ኮሌስትሮል፣ ግፊት፣ ስኳር፣ ሲጋራ) መጀመሪያ ምልክት የሚያሳዩት በብልት የደም ስሮች ላይ ሊሆን ይችላል።
- ለብዙ ወንዶች የስንፈተ ወሲብ ችግር መከሰት፣ ከ2 እስከ 5 ዓመታት በኋላ ለሚመጣ የልብ ድካም ወይም ስትሮክ ቀዳሚ ደወል ነው።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

5️⃣. መቼ ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል? 🏥🏃‍♂️

ከዚህ በታች ያሉት ምልክቶች ካሉ ከጤና ባለሙያ ጋር መማከር ያስፈልጋል፡
- የብልት መቆም ችግር በተደጋጋሚ ካጋጠመዎት
- ችግሩ ለ3 ወራት እና ከዚያ በላይ ከቆየ
- ችግሩ ውጥረት እና ጭንቀት ከፈጠረ።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

6️⃣. የህክምና አማራጮች 💊✅

ትክክለኛ እርዳታ ካገኙ አብዛኛዎቹ ወንዶች ወደ ነበሩበት መመለስ ይችላሉ። ህክምናው የሚከተሉትን ያካተተ ነው፡

1) የኑሮ ዘይቤን ማስተካከል 🏃‍♂️🥗
- ሲጋራ ማቆም (ይህ ትልቁ መፍትሄ ነው!)
- አልኮልን መቀነስ
- ከመጠን ያለፈ ክብደትን መቀነስ
- በየቀኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ (ፈጠን ያለ የእግር ጉዞ እንኳ የደም ዝውውርን ያሻሽላል)
- በቂ እንቅልፍ መተኛት እና ጭንቀትን ማስወገድ።
ለቀላል ችግሮች ይህ እርምጃ ብቻውን ትልቅ ለውጥ ያመጣል።

2) መሰረታዊ ህመሞችን ማከም 📉
- የስኳር መጠንን መቆጣጠር፣ ግፊት እና ኮሌስትሮልን ማስተካከል።
- የሆርሞን ማነስ ካለ በሐኪም ትዕዛዝ ማስተካከል።

3) ስነ-ልቦናዊ ምክር (S*x Therapy) 🗣️
በተለይ ጤናማ ለሆኑ ወጣቶች፣ የፍርሃት እና የጭንቀት አዙሪትን ለመስበር፣ ከትዳር አጋር ጋር መግባባትን ለመፍጠር እጅግ ይጠቅማል።

4) የሚዋጡ መድሃኒቶች (ክኒኖች) 💊
የብልት የደም ዝውውርን የሚጨምሩ መድኃኒቶች ።

5) የቫኪዩም መሳሪያዎች (Vacuum Devices) 🛠️
ያለ ቀዶ ጥገና እና ያለ መድሃኒት፣ ደም ወደ ብልት እንዲገባ የሚረዱ የፕላስቲክ መሳሪያዎች ናቸው።

6) በመርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶች 💉
ክኒን ለማይሰራላቸው ሰዎች፣ ከግንኙነት በፊት በትንሽ መርፌ የሚሰጡ መድሃኒቶች አሉ።

7) የቀዶ ጥገና ህክምና (Pe**le Implants) 🛏️
ሌሎች አማራጮች ሁሉ ሳይሰሩ ሲቀሩ በመጨረሻ የሚሰጥ ቋሚ የቀዶ ጥገና መፍትሄ ነው።

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

7️⃣ ለትዳር አጋሮች (ሚስቶች) ፡ እንዴት ማገዝ ይችላሉ? 👩‍❤️‍👨🤝

- እሱን ወይም ራስዎን ከመውቀስ ይቆጠቡ።
- "ይህን ችግር አብረን እንፈታዋለን" የሚል የጋራ ስሜት ይፍጠሩ።
- ወደ ሐኪም እንዲሄድ ያበረታቱት ፤ ከቻሉም አብረውት ይሂዱ።
- አፈፃፀም ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ በመተሳሰብ፣ በማውራት፣ እና በፍቅር ቅርበት መፍጠር ላይ ያተኩሩ።
የሚረዳ እና የሚረዳዳ የትዳር አጋር መኖር ለፈጣን መዳን ትልቁ መንገድ ነው!

〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️〰️

8️⃣. ማጠቃለያ መልእክት 💌
- ሃፍረት አይሰማዎት ፤ ባለሙያዎች ይህንን በየቀኑ ያዩታል።
- ያለሐኪም ትዛዝ በሚሸጡ ክኒኖች ራስዎን አያክሙ።

🏆 ዝም ብሎ በሃፍረት ከመሰቃየት ይልቅ፣ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዶ እርዳታን መጠየቅ ከምንም በላይ እውነተኛ ወንድነት ነው!

🙏Please follow Share and Like

Dr Abera Etana



​ #የወንዶችጤና #የብልትአለመቆም #ስንፈተወሲብ #ጤና #ጤናማህይወት *xualHealth

🧴 የፀጉር እና የፊት ላይ ፎረፎር (Seborrheic Dermatitis) 🧴ብዙዎቻችንን የሚያስቸግረውና በተለምዶ "ፎረፎር" የምንለው ይህ የቆዳ ችግር፣ በህክምናው Seborrheic Dermat...
01/03/2026

🧴 የፀጉር እና የፊት ላይ ፎረፎር (Seborrheic Dermatitis) 🧴

ብዙዎቻችንን የሚያስቸግረውና በተለምዶ "ፎረፎር" የምንለው ይህ የቆዳ ችግር፣ በህክምናው Seborrheic Dermatitis ይባላል። ይህ ህመም ተላላፊ አይደለም፤ ነገር ግን ተገቢው ክትትል ካልተደረገለት ደጋግሞ የመመለስ ባህሪ አለው።

🔍 ምልክቶቹ እና የሚጠቁ አካላት
ይህ ህመም የሰውነታችን የቅባት እጢዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ይከሰታል፡
📍 የራስ ቅል ቆዳ፦ ማሳከክ እና ነጫጭ ወይም ቢጫ ቀለም ያላቸው ቅርፋፊዎች።
📍 ፊት ላይ፦ በቅንድብ፣ በሽፋሽፍት፣ በጆሮ ጀርባ እና ከአፍንጫ ጎን (Nasolabial folds) የሚወጣ ቀላ ያለ እና የሚመረቅዝ ሽፍታ።
📍 ሌሎች፦ በጢም ውስጥ፣ በደረት እና በጀርባ መካከለኛ ክፍል ላይ።
🧬 ለምን ይከሰታል? (Causes & Triggers)
ምንም እንኳን ትክክለኛ መንስኤው ባይታወቅም፣ የሚከተሉት ነገሮች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡
🔹 ማላሳዚያ (Malassezia)፦ በቆዳችን ላይ የሚገኝ እርሾ መሰል ፈንገስ ከመጠን በላይ ሲራባ።
🔹 የአየር ንብረት፦ ቀዝቃዛ እና ደረቅ አየር ህመሙን ያባብሰዋል።
🔹 ጭንቀት (Stress)፦ ከፍተኛ የአእምሮ ውጥረት ለሽፍታው መባባስ ዋነኛው ምክንያት ነው።
🔹 የበሽታ መከላከል አቅም መውረድ፦ ለምሳሌ በኤች አይ ቪ (HIV) ወይም በፓርኪንሰን (Parkinson's) ህመም ምክንያት።

💊 ወቅታዊ የህክምና አማራጮች

1️⃣ ለራስ ቅል ፎረፎር (Scalp Treatment):
🧴 ፀረ-ፈንገስ ሻምፖዎች፦ Ketoconazole 2% ወይም Selenium Sulfide ያላቸውን ሻምፖዎች በሳምንት 2-3 ጊዜ መጠቀም።
⚠️ ወሳኝ ነጥብ፦ ሻምፖውን ከተቀቡ በኋላ አረፋውን ከ 5-10 ደቂቃ ማቆየት አለብዎት። ካልቆየ ፈንገሱን የመግደል አቅሙ ዝቅተኛ ይሆናል።
🧴 ስቴሮይድ (Steroids)፦ ከፍተኛ ማሳከክ እና መቅላት ካለ፣ ሀኪም የሚቀቡ ፈሳሽ ስቴሮይዶችን ሊያዝ ይችላል።
2️⃣ ለፊት እና ለሰውነት ሽፍታ (Face & Body):
🧴 Ketoconazole 2% Cream፦ በቀን 1-2 ጊዜ መቀባት።
🧴 Antifungal Wash፦ ጢም ላላቸው ወንዶች በኬቶኮናዞል ሻምፖ ፊትን መታጠብ ውጤታማ ነው።
🧴 Moisturizers፦ ቆዳ እንዳይደርቅና እንዳይቆጣ ጥንቃቄ ማድረግ።
🚫 ምን ማስወገድ አለብን?
❌ የጭቃ ቅባት (Pomade)፦ ቅባታማ የሆኑ የፀጉር ቅባቶች ፈንገሱ እንዲራባ ስለሚያደርጉ መጠቀም አይመከርም።
❌ ማከክ ፦ ማከክ ቁስለት በመፍጠር ለተጨማሪ ባክቴሪያ ኢንፌክሽን ያጋልጣል።
❌ አልኮል ያላቸው የፊት ሳሙናዎች፦ ቆዳን በማድረቅ ህመሙን ያባብሳሉ።
💡 የዶክተር ምክር
ይህ ህመም ሙሉ በሙሉ ጠፍቶ ላይመለስ ይችላል። ስለዚህ ምልክቱ ከጠፋ በኋላም ቢሆን በሳምንት አንድ ጊዜ በፀረ-ፈንገስ ሻምፖ መታጠብ ህመሙ ተመልሶ እንዳይመጣ (Maintenance therapy) ይረዳል።

ዶ/ር አበራ ኢታና (Dr. Abera Etana)

DrAbera Etana


#የቆዳጤንነት #ፎረፎር #የፀጉርጤንነት #ጤና #ኢትዮጵያ #ውበት #የቆዳህክምና #ዶክተርአበራ

🤰 በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት እና ፕሪኢክላምሲያ (Preeclampsia) 🩺👉በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት የእናትንና የፅንሱን ጤና አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ከፍተኛ ጥ...
01/03/2026

🤰 በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት እና ፕሪኢክላምሲያ (Preeclampsia) 🩺

👉በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት የእናትንና የፅንሱን ጤና አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄና የህክምና ክትትል ያስፈልገዋል።
🔍 ፕሪኢክላምሲያ (Preeclampsia) ምንድነው?

👉ፕሪኢክላምሲያ ብዙውን ጊዜ ከ20ኛው ሳምንት የእርግዝና ጊዜ በኋላ የሚከሰት፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እና በአንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ የሰውነት ክፍሎች (እንደ ኩላሊት፣ ጉበት ወይም አንጎል) ላይ የሚታይ የጤና መታወክ ነው።
🧬 መንስኤው ምንድነው? (Causes)
👉ትክክለኛው መንስኤ አሁንም በጥናት ላይ ቢሆንም፣ ዋናው መነሻ የክብሪት (Placenta) እድገት መዛባት እንደሆነ ይታመናል። ወደ ፅንሱ የሚሄዱ የደም ስሮች በጠባብነታቸው ምክንያት በቂ ደም ማስተላለፍ ሲያቅታቸው፣ የእናቲቱ አካል ግፊቱን በመጨመር ምላሽ ይሰጣል።

🚩 ለፕሪኢክላምሲያ ተጋላጭ የሆኑት እነማን ናቸው? (Risk Factors)
🔹 የመጀመሪያ እርግዝና
🔹 ቀደም ሲል የነበረ ስኳር፣ የኩላሊት ህመም ወይም የደም ግፊት
🔹 መንታ ወይም ከዚያ በላይ ፅንስ መሸከም 👶👶
🔹 እድሜ ከ35 ዓመት በላይ ወይም ከ20 ዓመት በታች መሆን
🔹 ከመጠን ያለፈ ውፍረት (BMI > 30)
🔹 ቀደም ባለው እርግዝና ፕሪኢክላምሲያ የነበረባት እናት

📋 ምርመራው እንዴት ይደረጋል? (Diagnosis)
ሀኪሞች ፕሪኢክላምሲያ መኖሩን የሚያረጋግጡት በሚከተሉት መስፈርቶች ነው፡
📍 ከፍተኛ የደም ግፊት፦ በሁለት የተለያዩ ጊዜያት ተለክቶ ከ 140/90 mmHg በላይ ሆኖ ሲገኝ።
📍 ፕሮቲን በሽንት ውስጥ (Proteinuria)፦ የኩላሊት መጎዳትን የሚያሳይ ምልክት።
📍 የላቦራቶሪ ውጤቶች፦ የፕሌትሌት (Platelet) መጠን መቀነስ፣ የጉበት ኢንዛይሞች መጨመር ወይም የኩላሊት ስራ መጓደል።

⚠️ የሚያስከትለው አደጋ (Dangers)
ይህ ሁኔታ በፍጥነት ካልታከመ የሚከተሉትን አደጋዎች ሊያስከትል ይችላል፡
🛑 ኢክላምሲያ (Eclampsia)፦ እናቲቱ ላይ ድንገተኛ የሚጥል በሽታ (Seizure) ማስከተል።
🛑 የፅንስ እድገት መገታት፦ ለፅንሱ የሚሄደው ደም እና ኦክስጅን በመቀነሱ ፅንሱ ሳይጠነክር መወለድ።
🛑 የክብሪት (Placenta) መላቀቅ፦ ፅንሱ ሳይወለድ በፊት ክብሪቱ ከማህፀን በመላቀቁ ምክንያት የሚመጣ ከባድ ደም መፍሰስ።
🛑 HELLP Syndrome፦ የቀይ የደም ሴሎች መፈራረስ እና የጉበት መጎዳት።

💊 የህክምና አማራጮች እና መከላከያ መንገዶች
✅ ዝቅተኛ መጠን ያለው አስፕሪን (Low-dose Aspirin)፦ ለፕሪኢክላምሲያ ተጋላጭ የሆኑ እናቶች ከ12ኛው እስከ 16ኛው ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ አስፕሪን መጀመር የግፊቱን የመከሰት እድል በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል።
✅ የማግኒዥየም (Magnesium Sulfate) ህክምና፦ ግፊቱ ወደ ሚጥል በሽታ እንዳይቀየር ለመከላከል የሚሰጥ ወሳኝ መርፌ ነው።
✅ አስቸኳይ ወሊድ፦ ብቸኛውና የመጨረሻው የፕሪኢክላምሲያ ህክምና ፅንሱ እንዲወለድ ማድረግ ነው።

🔔 ወሳኝ መልዕክት
📢 በእርግዝና ወቅት ግፊት የታየባቸው እናቶች ወሊዳቸው በሆስፒታል ብቻ መሆን አለበት።
📢 የረጅም ጊዜ ስጋት፦ በእርግዝና ወቅት ግፊት የነበረባቸው እናቶች ወደፊት ለልብ ህመም እና ለተከታታይ የደም ግፊት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከወሊድ በኋላም ክትትል ያስፈልጋቸዋል።
ለተጨማሪ መረጃ የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ። 🏥👨‍⚕️

DrAbera Etana


#የደምግፊት #እርግዝና #ጤና #ፕሪኢክላምሲያ #የእናቶችጤና #ኢትዮጵያ #ዶክተርአበራ #የእናቶችሞትይቀነስ

🧐🧬የቆዳ ሸንተረርን (Stretch Marks) ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይቻላል? ብዙዎቻችንን የሚያሳስበን የቆዳ ሸንተረር ጉዳይ በሳይንሳዊው እይታ ሲታይ እንዲህ ነው፡🔍 ሸንተረር እንዴት ይከሰታል?...
01/03/2026

🧐🧬የቆዳ ሸንተረርን (Stretch Marks) ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይቻላል?

ብዙዎቻችንን የሚያሳስበን የቆዳ ሸንተረር ጉዳይ በሳይንሳዊው እይታ ሲታይ እንዲህ ነው፡

🔍 ሸንተረር እንዴት ይከሰታል?
ቆዳችን ሊለጠጥ ከሚችለው አቅም በላይ በፍጥነት ሲለጠጥ የሚፈጠር ጠባሳ (Scar) ነው።
🔹 ፈጣን የክብደት መጨመር ወይም መቀነስ ⚖️
🔹 እርግዝና 🤰
🔹 በጉርምስና ወቅት የሚመጣ ፈጣን እድገት 📈
🔹 የስቴሮይድ (Steroid) ቅባቶችን ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ለረጅም ጊዜ መጠቀም ⚠️

🚫 እውነታው፡ ሙሉ በሙሉ ይጠፋል?

እንደማንኛውም ጠባሳ፣ ሸንተረርን ሙሉ በሙሉ (100%) የሚያጠፋ ተአምራዊ ቅባትም ሆነ ህክምና የለም። ነገር ግን እንዲደበዝዝ እና ከቆዳ ጋር እንዲዋሃድ ማድረግ ይቻላል! ✅
🩺 ውጤታማ የህክምና አማራጮች
ህክምናዎች ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑት ሸንተረሩ ገና እንደወጣ (Striae Rubra - ቀይ/ሐምራዊ ቀለም እያለው) ሲጀመር ነው።
📍 Microneedling: በደቃቅ መርፌዎች ቆዳን በማነቃቃት አዲስ ኮላጅን (Collagen) እንዲመረት ማድረግ።
📍 Laser Therapy: የጨረር ህክምና የቆዳን ቀለም እና መልክ ለማስተካከል።
📍 Chemical Peels: የላይኛውን የተጎዳ ቆዳ በማንሳት አዲስ ቆዳ እንዲተካ ማድረግ።
📍 Tretinoin Cream: የቆዳ ሴሎች ራሳቸውን እንዲያድሱ ይረዳል (ለአዳዲስ ሸንተረሮች)።
📍 Hyaluronic Acid: ቆዳ እርጥበት አግኝቶ እንዲለጠጥ በማድረግ ስር እንዳይሰድ ይከላከላል።
⚠️ ወሳኝ ጥንቃቄዎች
🛑 ለነፍሰ ጡሮች፡ Tretinoin የተባለውን መድኃኒት በፍፁም መጠቀም የለባችሁም! በፅንሱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ❌🤰
🛑 ማስታወቂያዎች፡ "በ3 ቀን ውስጥ ሸንተረርን እናጠፋለን" የሚሉ ቅባቶች በአብዛኛው ሳይንሳዊ መሰረት የሌላቸው እና ገንዘብ የሚያባክኑ ናቸው።
ባጠቃላይ፡ ሸንተረር የሰውነታችን የለውጥ ምልክት እንጂ የጤና ጠንቅ አይደለም። ህክምና ከፈለጉ ግን ወደ ቆዳ ሀኪም (Dermatologist) በመሄድ ትክክለኛውን መንገድ ይምረጡ። 🏥👨‍⚕️

Dr Abera Etana



#የቆዳጤንነት #የቆዳሸንተረር #ጤና #ኢትዮጵያ #ውበት #የቆዳህክምና

Address

ሐዋሣ/Hawassa
Awassa

Website

Alerts

Be the first to know and let us send you an email when Dr Abera Etana posts news and promotions. Your email address will not be used for any other purpose, and you can unsubscribe at any time.

Share