27/09/2025
የታደሰ የሙያ ፈቃድ ያልያዙ የጤና ባለሙያዎች
አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ተገለጸ
"No license,No practice"
| የጤና ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድን በሚመለከት በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ ተፈርሞ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁሉም ክልሎች የተላከው ደብዳቤ፤ "ሁሉም ክልሎች እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የንቅናቄ ስራ በመስራት ሁሉም ባለሙያ የሙያ ፍቃድ ይዞ እንዲሰራ እንዲደረግ አሳስባለሁ" ይላል።
"በመመሪያው መሰረት የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ሁሉም ባለሙያዎች የታደስ የሙያ ፈቃድ እንዲኖራቸው ይጠበቃል " ያለው የጤና ሚኒስቴር፤ ይህንንም ተከታትሎ ማስፈጸም በጤና ሚኒስቴር የጤናና ጤና ነክ ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈጻሚ መሆኑን ይገልጻል።
በ2017 በጀት ዓመት የጤና ሚኒስቴር ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሰረት፤ የሙያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ እንዲሁም የአገልግሎት ጊዜው ባለፈበት የሙያ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ባለሙያዎችን መኖራቸዉን ማረጋገጡን ገልጿል።
በዚህ መሰረት "ሁሉም የጤና ባለሙያዎች በሙያቸው ለመስራት የታደሰ የሙያ ፈቃድ መያዝ እንደሚያስፈልጋቸው ታውቆ፣ በክልላችሁ ስር በሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እስከ መስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም ብቻ የሙያ ፈቃድ እንዲያወጡ " ሲል ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
ከመስከረም 30 ቀን 2018 ዓ.ም በኋላ ግን "No license,No practice" በሚል መሪ ቃል፣ የሙያ ፈቃድ የሌላቸው ባለሙያዎች፣ በሙያቸው መስራት እንደማይችሉ አሳውቋል።
የሙያ ፈቃድ ለማውጣትና ለማሳደስ የተሰጠው ጊዜ እስከሚያልቅ ክልሎች አስፈላጊውን የንቅናቄ ስራ በመስራት፣ ሁሉም ባለሙያ የሙያ ፍቃድ ይዞ እንዲሰራ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ መሰጠቱን ቲክቫህ ጠቁሟል፡፡