26/05/2026
በሕዝብ ጤና ላይ የተደቀነ አደገኛ “የሕክምና ውንብድና/ማጭበርበር”
በአሁኑ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ ቦታዎች ራሳቸውን የተለያየ ስም በመሰየም፣ በሕጋዊ መንገድ የሚሰጠውን ዘመናዊ ሕክምና የሚያደናቅፉና የሰዎችን ሕይወት ለአደጋ የሚያጋልጡ አካላት በስፋት እየታዩ ይገኛሉ።
ይህ ድርጊት በሕክምናው ማኅበረሰብም ሆነ በሕዝብ ጤና ላይ ከፍተኛ ስጋት የሚፈጥር፣ በአስቸኳይ ሊታረም የሚገባው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሕዝብን ለማደናገር የሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል።
✅የዘመናዊ ሕክምና መረጃዎችን በማጣመም ሕዝብን ማደናገር
-እነዚህ አካላት መረጃ የሚያደርጉትና ንግዳቸውን የሚያስፋፉበት ዋነኛው ስልት የዘመናዊ ሕክምና ምርምሮችን በግርፉ በማንበብ፣ ሳይንሳዊ ቃላትን እየቀላቀሉ የራሳቸው የፈጠራ ግኝት አስመስሎ ማቅረብ ነው።
✅የመረጃ ምንጭ ማጭበርበር፦ -በሳይንስ የተረጋገጡ የሕክምና መመሪያዎችን (Guidelines) በማጣመም፣ ሕዝቡ በዘመናዊው የሕክምና ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸርና ወደ እነሱ እንዲመጣ ያደርጋሉ።
✅የተሳሳተ መረጃ (Misinformation)፦ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ከግል ጥቅም ጋር በማቀናጀት፣ ለከባድ እና ስር ለሰደዱ በሽታዎች የተሳሳቱና አደገኛ መላምቶችን ያሰራጫሉ።
✅መድኃኒቶችን እንደ ሸቀጥ ማስተዋወቅ፦ የጤና ጥፋት!
መድኃኒቶችን ልክ እንደ ልብስ ወይም ሸቀጥ ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ "እኛ ጋ አለ ሸምቱ" ብሎ ማስተዋወቅ እጅግ አሳፋሪ እና አደገኛ ስግብግብነት ነው። ከ "over the counter" ከሚባሉት መድኃኒቶች በስተቀር ጥብቅ የሕክምና ክትትል፣ የላብራቶሪ ምርመራ እና ትክክለኛ የመጠን ማስተካከያ የሚፈልጉ ናቸው።
እነዚህ መድኃኒቶች ያለ ሐኪም ትዕዛዝ እና ክትትል ሲወሰዱ ብዙ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ። ሕክምና በጨረፍታ በማንበብና በማኅበራዊ ሚዲያ ጩኸት የሚመራ ሳይሆን፣ ዓመታትን በፈጀ ትምህርት፣ በምርምር እና በሕጋዊ ተጠያቂነት የሚሰራ የተከበረ ሙያ ነው።
እንደ ምሳሌ
👉በስኳር፣ ግፊት እና ኮሌስትሮል ታካሚዎች ላይ የሚሰነዘር "የሕክምና ውንብድና"
ስኳር፣ ደም ግፊት እና የኮሌስትሮል መዛባት በሕክምናው ዓለም "ዝምተኛ ገዳዮች (Silent Killers)" በመባል ይታወቃሉ። የህመሙ ጉዳት እና ጠንቅ ወዲያውኑ ላይታይ ይችላል። እነዚህ በሽታዎች በሳይንሳዊ መንገድ በታዘዙ መድኃኒቶች እና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ካልተቆጣጠሯቸው በስተቀር በሰውነት ውስጥ ያሉትን የደም ስር ቧንቧዎችና የውስጥ አካላትን ቀስ በቀስ ይጎዳሉ።
እነዚህ አካላት ጭራሽ "የስኳር፣ የግፊት እና የኮሌስትሮል ታካሚዎች መድኃኒት መውሰድ የለባችሁም" እያሉ ሕዝቡን ማወዛገባቸው ትልቅ ወንጀል ነው። ማንኛውም ሰው የሕክምና ዶክትሬት ዲግሪ እና የሙያ ፈቃድ (License) ሳይኖረው የመድኃኒት መጠን የመወሰን፣ የመቀየር ወይም የማቋረጥ መብት የለውም።
መድኃኒት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ የስኳር መጠን፣ የግፊት ልኬት፣ እንዲሁም የኮሌስትሮል መጠን ሊጨምር ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የጭንቅላት ደም መፍሰስ (Stroke) ወይም ድንገተኛ የልብ ድካም (Heart Attack)፣ ለኩላሊት ሥራ ማቆም፣ ለዓይን ብርሃን መጥፋትና ለነርቭ መጎዳት እና ሌሎችም ይዳርጋል።
"መድኃኒት አያስፈልግም፣ እኛ ብቻችንን ያለ መድሀኒት እናክማለን" ማለት የሰዎችን ሕይወት መጫወቻ ማድረግ እና ከባድ የሕክምና ውንብድና ነው።
👉ትክክለኛው አሰራር፦ የስነ-ምግብ ምክር እና ሌሎች ሕክምና በጋራ መስራት (Multidisciplinary Approach)
-የስነ-ምግብ (Nutrition) አገልግሎት እና ተገቢ የአኗኗር ዘይቤ ለስኳር፣ ለግፊት እና ለኮሌስትሮል ሕክምና ወሳኝ የሆኑ የሕክምናው ክፍሎች ናቸው። ነገር ግን ይህ አገልግሎት ውጤታማ የሚሆነው በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ ሲመራ ብቻ ነው፦
-የጋራ ሥራ (Collaboration)፦ በሕጋዊ መንገድ የሚሰሩ እውነተኛ የስነ-ምግብ ባለሙያዎች ከታካሚው ዋና ሐኪም (ለምሳሌ ከስኳር እና ሆርሞን ሀኪም) ጋር በጋራ በመወያየትና በመመካከር ነው የሚሰሩት። የሐኪሙን የሕክምና እቅድ እና የታካሚውን የላብራቶሪ ውጤት መሠረት በማድረግ ተስማሚ የምግብ ሥርዓት ይቀይሳሉ። በዚህ መልኩ በጋራ በመሥራት ጥሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
-መደጋገፍ እንጂ መተካካት አይደለም፦ ጤናማ አመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤ ለውጥ መድኃኒቶችን ይደግፋሉ፣ ውሎ አድሮም የመድኃኒቱን መጠን ለመቀነስ ሊረዱ ይችላሉ፤ መድሀኒቶች የታዘዙበት ምክንያትም የስኳርን ወይም የደም ግፊትን መጠን ከመቀነስ በተጨማሪ ብዙ የጤና ጠንቆችን እና ሞትን ለመቀነስ ታሳቢ ተደርጎም ነው።
-ወሰንን (Scope of Practice) ማወቅ፦ ሳይንሳዊ ሥነ-ምግባር ያላቸው እውነተኛ ባለሙያዎች የራሳቸውን የሙያ ወሰን (Scope of Practice) ያውቃሉ። መድኃኒት የመቀየርም ሆነ የማቆም ሥልጣን የዋናው ህጋዊ ሐኪም ብቻ መሆኑን አምነው ይቀበላሉ። የአንድ ህመም የሚሰጠውን የመድሀኒት ስም ማወቅ ማለት መድሀኒቱ መስጠት ይችላል ማለት አይደለም።
ለምሳሌ አንድ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት አንዲት እርጉዝ ሴት ምጥ ሲዘገይ እንደ አስፈላጊነቱ የምጥ መርፌ (Oxytocin) ሊሰጥ እንደሚችል ያውቃል፤ ነገር ግን ሄዶ አያዝም (የማሕፀንና ፅንስ ሐኪሙ ሙያ ስለሆነ)። የማህፀን ሀኪሙም የውፍረት መቀነሻ መድሀኒት ስም ስላወቀ የውፍረት ህመምን ያክማል ማለት አይደለም። በተመሳሳይ፣ የስነ-ምግብ ባለሙያ የስኳር ሕመም መድኃኒት ስሙን ስላወቀ ብቻ መድኃኒት ማዘዝም ሆነ ማቋረጥ የለበትም።
✅ማጠቃለያ
ታካሚዎች በማኅበራዊ ሚዲያ በሚደረጉ የሀሰት ማስታወቂያዎች በመታለል የጀመሩትን መድኃኒት ከሐኪም ጋር ሳይመካከሩ ማቋረጥ የለባቸውም። ግልጽ የሆነ ውይይት እና በጋራ በሚቀመጥ የሕክምና አቅጣጫ ያስፈልጋል።
ትክክለኛ የትምህርት ዝግጅት ሳይኖራቸው ራሳቸውን የተለያየ ስም በመሰየም አዳዲስና ጥንቃቄ የሚሹ መድኃኒቶችን እንደ ሸቀጥ የሚቸረችሩ እና መድኃኒት አስቁመው በሰዎች ሕይወት ላይ የሚቀልዱ ግለሰቦች ዝም ሊባሉ አይገባም፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጤና ቁጥጥር አካላት አፋጣኝ እርምጃ ሊወስዱበት ይገባል።
ዶ/ር ክብረት እንየው: የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት እንዲሁም የስኳር እና የሆርሞን ህመም ሰብ-ስፔሻሊስት
ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ
Telegram: t.me/HakimEthio