26/08/2026
ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል የክረምት በጎ ፈቃድ የህክምና አገልግሎት መስጠቱን ቀጥሏል!
በዛሬው እለትም የክረምት በጎ ፈቃድ የሕክምና አገልግሎት ስራው በድሬዳዋ አስተዳደር በተለያዩ አካባቢዎችና መርሃ ግብሮች ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአሳሊሶ ክላስተር ለማህበረሰቡ ነፃ የሕክምና ምርመራ፣ የጤና ምክርና የጤና ትምህርት አገልግሎቶች ተሰጥዋል። በሌላ በኩልም፣ በቦረን የወላጅ አልባ ሕፃናት ማቋቋሚያ ማዕከል (Orphan Rehabilitation Center) የሕፃናት ሕክምና ስፔሻሊስቶች ለሕፃናት የተለያዩ የሕክምና አገልግሎቶችን ሰጥተዋል። እንዲሁም በቦረን ጤና ጣቢያ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቶች ለእርግዝና ክትትል ለመጡ እናቶች የአልትራሳውንድ ምርመራና ሌሎች ተያያዥ የሕክምና አገልግሎቶችን ሰጥተዋል።
በምርመራው ወቅትም ተጨማሪ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው፣ የስኳር ሕመምና የደም ግፊት ያለባቸው፣ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ ተጨማሪ ሕክምና የሚያስፈልጋቸዉ እናቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ሕክምናዎች የሚያስፈልጋቸው ሕፃናቶች ወደ ሆስፒታላችን በሪፈራል ተልከው ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።
የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሁሴን መሀመድ በበኩላቸው፣ የክረምቱ በጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ንቅናቄና ማነቃቂያ እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዉ፤ይህም የሕክምና ምርመራዉ በክረምት ወቅት ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድ እንደ ባህል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል። በመጨረሻም በተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ ማህበረሰቡን በማስተባበርና ለስራዎቹ ስኬት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።።
ለጤናችን በጋራ እንሠራለን!!!
(ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል)
ነሐሴ 20/2018 ዓ.ም