16/04/2026
Via; Ministry of Health,Ethiopia
ለ175 የልብ ህሙማን ህጻናት ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ለመስጠት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ
__________
የመግባቢያ ሰነዱ በጤና ሚኒስቴር እና የልብ ቀዶ ህክምና አጋር በሆኑ የግል እና የመንግስት ሆስፒታሎች የተፈረመ ሲሆን፤ ነጻ የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው ከሚያዝያ 12 ጀምሮ ለ45 ቀናት በግል እና በመንግስት ሆስፒታሎች የሚሰጥ ይሆናል።
የመግባቢያ ሰነዱን ከጤና ሚኒስቴር ጋር የተፈራረሙት የኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ፣ የኢትዮጵያ የልብ ማህበር፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የቅዱስ ዼጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የኢትዮ-ኢስታንቡል ሆስፒታል፣ የኤልውዘር የልብ ህክምና ማዕከል እና የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ናቸው።
የልብ ቀዶ ህክምና ዘመቻው በዘርፉ ያለውን ጫና ለማቃለል የጎላ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት በትብብር ሲሰሩ ዘለቄታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ገልፀው፣ የመግባቢያ ሰነዱን የፈረሙ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እና ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶ/ር ሙሉቀን ተስፋዬ እና የኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ ድርጅት መስራች አቶ ብርሀን ተድላ የመንግስት እና የግል ዘርፍ በትብብር መስራት እውቀትን፣ ልምድን እና ሀብትን በመካፈል ሀገራዊ የልብ ህክምና አቅምን ለመገንባት ይጠቅማል ብለዋል።
በተጨማሪም በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለ20 የልብ ህሙማን ህጻናት ህክምናው የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህም በአጠቃላይ አገልግሎቱን የሚያገኙ ህጻናት ቁጥርን ወደ 195 ከፍ ያደርጋል፡፡
ለነፃ የልብ ህክምና ዘመቻ የሚውለው ግብዓት በኸርት ቱ ኸርት ችልድረን ኤይድ ድርጅት የሚቀርብ ይሆናል።
Website: moh.gov.et
Facebook: Ministry of Health,Ethiopia
Twitter: x.com/fmohealth
YouTube: youtube.com/
Tiktok: tiktok.com/
Telegram: t.me/M0H_EThiopia
Linkedin: lnkd.in/ewFJ6VAB