05/09/2026
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ 251 የጤና ባለሙያዎችን አስመረቀ
የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በ9ኛ ዙር በተለያዩ የጤና ሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 251 የጤና ባለሙያዎች ዛሬ ነሐሴ 30 2018 ዓ.ም አስመርቋል።
በምርቃት ስነ- ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊዎች ዶክተር ዱሬቲ ጀማል እና ዶክተር ሙሉጌታ እንዳለ ፣ የሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አበበ ታደሰ እና ምክትል ፕሮቮስቶች ፣ የኮሌጁ የሴኔት አባላት ፣ የጤና ቢሮ የማኔጅመንት አባላት ፣ የሆስፒታል ኮሌጁ ኃላፊዎች እና መምህራን ፣ ተመራቂዎች እና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል ።
የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ በሕክምና ዶክትሬት፣ በነርሲንግ፣ በሕክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ፣ በስፔሻሊቲ፣ በሰብስፔሻሊቲ እና በሕዝብ ጤና ማስተርስ ፕሮግራሞች የሰለጠኑ ተመራቂዎችን አካቷል።
የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ፕሮቮስት ዶክተር አበበ ታደሰ በሰጡት መልዕክት ኮሌጁ ለ103 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ አበርክቶ ያደረገ ታሪካዊ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮም 1,223 ብቁ የጤና ባለሙያዎችን ማፍራቱን ጠቁመዋል።
ዋና ፕሮቮስቱ ኮሌጁ ከቅድመ ምረቃ የሕክምና ዶክትሬት ሥልጠና ጀምሮ ዛሬ ላይ ስፔሻሊቲና ሰብስፔሻሊቲን ጨምሮ 21 ፕሮግራሞችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ኮሌጁ በጤና ሙያ ሥልጠና ያለውን አቅም እያሳደገ መምጣቱን አመላክቷል።
በዚህ ዙር ኮሌጁ በነርሲንግና በሕክምና ላቦራቶሪ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያስመርቅ፣ በአኔስቴዚያና ክሪቲካል ኬር ሜዲሲን ስፔሻሊቲ እንዲሁም በዩሮጋይኔኮሎጂ ሰብስፔሻሊቲ የመጀመሪያ ተመራቂዎችን አፍርቷል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዱሬቲ ጀማል በበኩላቸው የከተማዋ የጤና ዘርፍ በበሽታ መከላከል፣ በሕክምና አገልግሎት፣ በዲጂታላይዜሽን እና በጤና ተቋማት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የዛሬ ተመራቂዎችም የጤና ሙያ የሚጠይቀውን ርህራሄ፣ ታማኝነትና ቀጣይነት ያለው የአቅም ማሳደግ በመከተል ለሕሙማንና ለማኅበረሰቡ በትጋት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂዎች የኮሌጁን የትምህርትና የሙያ እሴት ይዘው ወደ ጤና ሥርዓቱ የሚቀላቀሉ በመሆናቸው፣ የምርቃቱ ቀን ለኮሌጁ የስኬት መጠናቀቂያ ሳይሆን ለተመራቂዎቹ የሙያ ሀላፊነት መጀመሪያ መሆኑ ተገልጿል።
በምርቃቱ ላይ ተመራቂ ሐኪሞችና የነርሲንግ ተመራቂዎች የሙያ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። በየሙያ ዘርፉ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎችም እውቅናና ሽልማት ተበርክቷል። በሕክምና ዶክትሬት የወርቅ ሜዳሊያ ያገኙት ዶክተር ይርጋለም መሐመድ ዩሱፍ 3.90 ውጤት አስመዝግበዋል።
የምርቃት ሥነ ሥርዓቱ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ታሪካዊ አበርክቶን ከቀጣይ ትውልድ የጤና ባለሙያዎች ጋር ያገናኘ ሲሆን፣ 252ቱ ተመራቂዎች የተማሩትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም ለሕሙማን፣ ለማኅበረሰቡ እና ለሀገሪቱ የጤና ሥርዓት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሙያ ጉዞአቸውን ጀምረዋል።
📍 የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ኮሚኒኬሽን
📅 ነሐሴ 30/2018 ዓ.ም
📍
📌 Follow Us on Social Media
👉 Facebook:
https://www.facebook.com/profile.php?id=100063650457050
👉 Telegram: Join Our Channel https://t.me/Y12HMCC
👉 Follow us on tiktok
https://vm.tiktok.com/ZMHWJyPGKQmQp-dftjE
🔖 💛✨