11/08/2026
"936 ታካሚዎች ከፍተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት አግኝተዋል፣ለ2788 እናቶች የወሊድ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን 446 ወላድ እናቶች ደግሞ በቀዶ ጥገና (Cs) በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲወልዱ ተደርጓል" አቶ አለአምላክ ተስፋ የደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ
ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም በ05/12/18 ገመገመ።
(ደባርቅ 05/12/18)
ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ አካሂዷል። በግምገማው የሆስፒታሉ የማኔጅመንት አባላት፣ ኬዝ ማናጀሮች፣ የክፍል አስተባባሪዎች፣ የስራ ሂደት መሪዎች፣ ፎካል ፐርሰኖች እንዲሁም ከየስራ ክፍሉ የተጋበዙ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ያቀረቡት የፕላንና ፕሮግራም ባለሙያ የሆኑት አቶ ሐዋርያት ማሙዬ ሲሆኑ በሪፖርታቸው ሆስፒታሉ በ2018 በጀት ዓመት ውስጥ ለ89,723 ተመላላሽ ታካሚዎች ህክምና መስጠቱን ገልጸዋል፤ ይህ አሃዝ ሆስፒታሉ ለማህበረሰቡ ካለው ተደራሽነትና ተቀባይነት አንጻር በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ያመላክታል። በተጨማሪም ለ936 ታካሚዎች ከፍተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት፣ ለ223 ታካሚዎች ደግሞ መለስተኛ የቀዶ ጥገና አገልግሎት መሰጠቱን አብራርተዋል፤ ይህም ሆስፒታሉ ውስብስብና ደረጃውን የጠበቀ የቀዶ ህክምና አገልግሎት በመስጠት የታካሚዎችን ህይወት እየታደገ መሆኑን ገልፀዋል።
በእናቶችና ህጻናት ጤና ረገድ፣ ለ2197 ነብሰጡር እናቶች የእርግዝና ክትትል፣ ለ2788 ወላድ እናቶች የወሊድ አገልግሎት፣ እንዲሁም ለ446 ወላድ እናቶች በቀዶ ጥገና (CS) የመውለድ አገልግሎት መሰጠቱ ተጠቅሷል። የCS ወሊድ መጠን መጨመር በአንድ በኩል ውስብስብ የወሊድ ጉዳዮችን በወቅቱ የመለየትና ህይወት የማዳን አቅምን የሚያሳይ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተቋሙ በቂ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ባለመኖሩ በተወሰነ የሰው ኃይል ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ አመላካች ነው። ለዚህም የሆስፒታሉ የተቀናጀ የድንገተኛ የቀዶ ጥገና ባለሙያ የሆኑት IESO ማሙሽ አቡሃይ በ2018 ዓመቱን ሙሉ ለ24 ስዓት ያለእረፍት በሆስፒታሉ ውስጥ ውለው በማደር ለእናቶችና ድንገተኛ አደጋ ለደረሰባቸው ሁሉ የህክምና አገልግሎት በመስጠታቸው ሆስፒታሉ ታላቅ ምስጋና በተቋሙና በህዝብ ስም አቅርቦላቸዋል። በሪፖርቱ ለ385 በፅኑ ህመም ለተያዙ ጨቅላ ህጻናት ህክምና መሰጠቱም ተጠቅሷል፤ ይህ የኒዮናታል ኬር አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ያሳያል።
ሪፖርቱ አክሎም ለ217 ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ ማግኘታቸውን፣ ለ4275 ታካሚዎች የዓይን ህክምና መሰጠቱን፣ለ136 ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማግኘታቸውን፣ ለ2059 የስነ አዕምሮ ታካሚዎች የህክምና አገልግሎት መሰጠቱን፣ ለ4010 ታካሚዎች ከ3 ቀናት በላይ በሆስፒታሉ ተኝተው ህክምና ማግኘታቸውን፣ ለ10,222 የድንገተኛ ህክምና ላስፈለጋቸው ታካሚዎች በድንገተኛ ክፍል ህይወት አድን ህክምና መሰጠቱን ገልጿል፤ ይህ ከፍተኛ ቁጥር ተቋሙ ያለበትን የስራ ጫናና ለድንገተኛ ጉዳዮች ያለውን ዝግጁነት በግልጽ ያመላክታል።
በተጨማሪም ለ998 የART ህክምና ተከታታዮች እና ለ77 የቲቢ ታካሚዎች ሙሉ ህክምና መሰጠቱን፣ ለ3716 ህፃናት የክትባት አገልግሎት ማግኘታቸውን፣ ለ2522 ተገልጋዮች የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በተለያዩ አማራጮች መሰጠቱ ተጠቅሷል፤ እነዚህ አገልግሎቶች የተላላፊ በሽታ መከላከልና የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ዘላቂነትን ከማረጋገጥ አኳያ ወሳኝ ናቸው።
ከጎንደር ደም ባንክ ጋር በመተባበር 470 ከረጢት ደም ደባርቅ ላይ መሰብሰቡ እና ከዚህ ውስጥ 382 ከረጢት ደም ለደም ማነስና ለደም መፍሰስ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች በደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ውስጥ መለገሱ ተገልጿል፤ ይህም ሆስፒታሉ ከአካባቢው የደም ባንክ ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ያመለክታል።
የሆስፒታሉ ዓመታዊ የፋይናንስና የግዥና የንብረት አስተዳደር ሪፖርት በስራ ሒደት አስተባባሪ በሆኑት በአቶ ቴዎድሮስ ሙሉሰው ቀርቧል። በሪፖርቱም ጥቅል የበጀት አጠቃቀም እና የግዥ ሪፖርት ቀርቧል። በተጨማሪም ሆስፒታሉ በዓመቱ የ 20,264,053.53 ብር የመድኃኒት ግዥ የተፈፀመ ሲሆን የ 15,823,235.64 ብር የሚያወጡ የተለያዩ መድኃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎች ሆስፒታሉ በድጋፍ ከአጋር አካላት በድጋፍ ያገኘ ሲሆን የ 5,050,010.62 ብር ነፃ የህክምና አገልግሎት ለወላድ እናቶችና ለህፃናት ተሰጥቷል፣ ለጤና መድህን ተጠቃሚዎች የ 18,603,143.16 ብር የሚያወጣ ህክምና ተሰጥቷል፣ የተሽከርካሪ አደጋ ለደረሰባቸው ድንገተኛ የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የ 318,969.50 ብር ነፃ የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል፣ ለተፈናቃዮች እና ለፀጥታ አስከባሪ አባላት የ 792,024 ብር የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል፣ ለጤና ሴክተር ሰራተኞች የ 374,274.99 ብር ህክምና የተሰጠ መሆኑ ተገልጿል።
የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ደግሞ በፕላንና ፕሮግራም አስተባባሪ በሆኑት በአቶ ማሙዬ ገ/መድኅን ቀርቧል።
የቀረቡትን ሪፖርቶች እና ዕቅድ መሰረት በማድረግ የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለአምላክ ተስፋ እና ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ፍቃዴ አማረ ተሰብሳቢዎችን ያወያዩ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹ የተቋሙን አገልግሎት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ሐሳቦችን፣ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አቅርበዋል። አቶ አለአምላክ ተስፋ "በውስን የሰው ኃይል ለ936 ሰዎች ከፍተኛ የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠታችን፣ 446 ወላድ እናቶች በቀዶ ህክምና በደባርቅ ሆስፒታል እንዲወልዱ ማድረጋችን እና እያንዳንዱ የተሰጠው የጤና አገልግሎት የሚያመላክተው ሆስፒታሉ ምን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰዎችን ህይወት እየታደገ እንዳለ ያሳያል" ብለዋል።
በሆስፒታሉ የሰው ኃይል እጥረት ቢኖርም ይህን ያህል ውጤት ማስመዝገብ የተቋማዊ አመራርና የሰራተኞች ቁርጠኝነት ውጤት በመሆኑ ለተቋሙ ባለሙያዎችና ሰራተኞች በሙሉ በተቋሙና በህዝብ ስም ለሰጡት ውጤታማ አገልግሎት ታላቅ ምስጋና እንደሚገባቸው ተገልጿል። ሆስፒታሉ ዘላቂ አገልግሎት አሰጣጥን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ስፔሻሊስት ባለሙያዎችን የማሟላት አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል። ሆስፒታሉ የተሟላ የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስት ሐኪም፣ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ ሐኪሞች ቢሟሉለት ከዚህ በላይ መስራት የሚችል፣ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለሀገር ትልቅ የህክምና አገልግሎት የሊሰጥ ተቋም መሆኑን በመግለጽ፣ ከተሰብሳቢዎቹ የተነሱ ጉዳዮች በመድረክ መሪዎቹ ሰፊ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።
በመጨረሻም የሆስፒታሉ መሪዎች፣ ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ከመንግስት በሚመደብለት በጀት፣ በውስጥ ገቢ ከሚሰበስበውና ከህዝብ ተሳትፎና ከአጋር አካላት የሚሰበሰብ ሀብትን በመጠቀም ሆስፒታሉን ለታካሚዎችና ለተቋሙ ሰራተኞች ምቹ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው፣ ለ2019 ዓ.ም ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ዝርዝር የስራ ዕቅዶች፣ መመሪያዎችና አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።
ደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል ለስሜን ጎንደር ህዝብ ከፍተኛውን የጤና አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም በመሆኑ ሆስፒታሉ በ2019 ዓ.ም የጤና መረጃ አያያዙን ዲጂታላይዝ ለማድረግ፣ የመድኃኒት እጥረትና የላቦራቶሪ ምርመራዎች ለማሟላት፣ የሰው ኃይል እጥረትን ለመፍታት በተለይም የከፍተኛ ስፔሻሊስት ሐኪሞችንና ጠቅላላ ሐኪሞችን (ሜዲካል ዶክተሮችን) ለማሟላት፣ ሙያተኞች የሚያነሷቸው የመብትና የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች እንዲመለሱ፣ ሆስፒታሉ መብራት ሲጠፋ ከነዳጅ ተጠቃሚነት ተላቆ የሶላር ኢነርጅ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ ደረጃውን የጠበቀ ማስፋፊያ ግንባታ እንዲደረግለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሆስፒታሉ የሚሰጠውን ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ከዚህ በላይ ማስቀጠል እንዲችል ከፍተኛ እገዛና ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።